Popular Posts

Wednesday, April 15, 2015

በአባያና ጫሞ ሐይቅ ያለውን የአሳ ሀብት ደህንነት ለመጠበቅ የጋራ ስራ ያስፈልጋል

ከአባያና ጫሞ ሐይቅ የሚገኘውን የዓሳ ምርት ለማሳደግ በሐይቆቹ ደህንነት ላይ የሚሰሩ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የጋሞ ጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ። ባለፉት ስምንት ወራት ማህበራትና አርሶ አደሮች ካቀረቡት ሁለት ሺህ 571 ቶን የዓሣ ምርት ከ115 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገቢ መገኘቱን ገልጿል።
 የዙኑ ግብርና መምሪያ የእንስሳት እርባታና መኖ ልማት የስራ ሂደት ተወካይ አቶ አቶ አንተነህ ጌታቸው ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ከሐይቆቹ የሚመርተውን የዓሳ ምርት መጠንና ጥራት ለመጨመር የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ዘንድሮ የተገኘው ምርት ካለፈው አመት ከ50 ቶን በላይ ብልጫ ቢኖረውም የሐይቆቹ የማምረት አቅም ከአምስት አመታት በፊት ከሚመረተው ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው በጣም ቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ የሐይቆቹ ደህንነት በአግባቡ እየተጠበቀ አለመሆን፣በሐይቆቹ ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ተሳትፎ ዝቅተኛ ስለሆነ ነው ብለዋል።
 በስምጥ ሸለቆ በዓሳ ምርት ክምችት የሚታውቀው የጫሞ ሐይቅ ብቻውን በዓመት ከ45 ሺህ ቶን በላይ፣አባያ ሐይቅ ደግሞ 3 ሺህ 500 ቶን ዓሣ የማምረት አቅም እንዳላቸውም ገልጸዋል። በተለይ በምርት ክምችቱ የሚታውቀው ጫሞ ሐይቅ በህገ ወጥ ዓሳ አስጋሪዎች መጨናነቁና ህገ ወጥ እርሻ መስፋፋት በአሳ ጫጩቶችና ዝሪያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
 ሐይቆቹን ከደለል በመከላከል የውሀ መጠኑን ለመጨመር በጋሞ ከፍተኛ አከባቢ በተከናወነው ተፋሰስ ልማት ሐይቆችን የሚመገቡ ገባር ወንዞች መጠን ቢጨምርም የሐይቆቹ ዙሪያ ወሰን ባለመከለሉ ህገ ወጥ አስጋሪነትን መከላከል ካልተቻለ በተፋሰስ ልማት ብቻ ውጤታማ እንደማይሆን ገልጸዋል።
 በአርባምንጭ ከተማ የዓሣ ምርት ተጠቃሚዎች በበኩላቸው ይመረታል የተባለው ዓሣ በከተማው የግብይት ማዕከላት ስለማይቀርብ መጠቀም እንዳልተቻለ ገልጸዋል። የሸቻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አባቡ መላኩ እንደተናገሩት አርባምንጭና አካባቢው ቀደም ሲል በዓሳ ምርት ቢታወቅም ጥራት ያለው ዓሳ የሚሸጥበት የግብይት ማዕከል እንደሌለ አስታውቀዋል። “የዓሳ ግብይቱ በአምራቾችና ንግድ ቤቶች እንዲተሳሰሩ ተደርጓል፣ ንግድ ቤቶቹም በአንድ ከተማ ውስጥ የሚሸጡበት ዋጋ የተለያየ ነው፣ ዓሣ በብዛት እየተመረተ ለስጋ ሉካንዳ ቤት እንደሚከፈት ለዓሣ መሸጫ ቦታ ለምን አይመቻችም ” ሲሉ ጠይቀዋል። ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ማሞ በአሁኑ ወቅት አሳን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቀሙ ገልጸው ምሽት ላይ በኮንትሮባንድ ካልሆነ በቀር ዓሳ የሚገዙበት ህጋዊ ማዕከል እንደሌለ አስታውቀዋል።
ሆሎች፣ንግድ ቤቶችና ዓሣ ከአምራች የሚረከቡ ግለሰብ ነጋዴዎች ምርቱን ወጥ በሆነ ዋጋ እንደማይሸጡ አስታውቀው ለህብረተሰቡ ግን በህጋዊ መንገድ የሚሸጡ የጅምላና ችርቻሮ መሸጫ ቦታዎች መመቻቸት እንደሚገባ ገልጸዋል። የዞኑ ግብይትና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እልፍነሽ ያፖ ህገ ወጥ አሣ አስጋሪዎችን ለመከላከል ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የሐቆቹንን መጨናነቅ ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት ስምንት ወራት በዓሳ ምርት በተሰማሩ ማህበራትና አርሶ አደሮች ሁለት ሺህ 571 ቶን የዓሳ ምርት ለገበያ በማቅረብ ከ115 ሚሊዮን 695 ሺህ ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።
በህጋዊ ዓሳ አስጋሪ፣አቅራቢና ችርቻሮ ላይ በተሰማሩ ከስምንት በሚበልጡ ህብረት ስራ ማህበራትና ከ40 የሚበልጡ የግል ሰራተኞች ከ15 በላይ ቸርቻሪዎችና ንግድ ቤቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። የአከባቢው ተጠቃሚ ምርቱን የሚያገኝበት ዘመናዊ የግብይት ማዕከል ከመፍጠር አንጻር ክፍተቶች እንዳሉ አስታውቀው በአርባምንጭ ከተማ የችርቻሮ ሱቆችን ለማስፋፋት ጥናት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። ከአስተዳደርና ንግድ እንዱስትሪ ተቋማት እውቅና ውጭ በህገ ወጥ መንገድ ዓሳ ለማስገር የተሰማሩ ከ200 የሚበልጥ መረቦችን በመለየት እንዲቃጠል ማድረጉን ገልጸዋል።
የሐይቆቹን ደህንነት ለማስጠበቅ የዞን፣የወረዳና ቀበሌ መዋቅር፣ በዓሳ መምረትና ማጓጓዝ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላትና አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ውይይት ለማካሄድ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑንም ወይዘሮ እልፍነሽ አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment