የኢዴፓ ነባር አመራር የነበሩት አቶ መስፍን መንግሥቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ነባር አመራሮች አንዱ የነበሩት አቶ መስፍን መንግሥቱ ተንሸራተው በመውደቃቸው ሳቢያ ሕይወታቸው በማለፉ፣ መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ተፈጸመ፡፡
አቶ መስፍን በተለያዩ ርዕስ ጉዳዮች ላይ ሪፖርተርን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሐሳባቸውን በማካፈል የሚታወቁ ፖለቲከኛ የነበሩ ሲሆን፣ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ የኢዴፓ አባል በመሆን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሠርተዋል፡፡ ለአምስት ዓመታት ያህል የኢዴፓ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ ለአምስት ዓመታት ያህል ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የምርጫ ክልል በምርጫ 97 አሸንፈው ከ1998 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነውም ሠርተዋል፡፡ በዚህ ቆይታቸው የመንግሥት ወጪዎች አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሆን የአቶ መስፍን ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡ አቶ መስፍን የኢብኮ (የያኔው ኢቲቪ) የቦርድ አባልም ነበሩ፡፡
አርባ ምንጭ አካባቢ የተወለዱት አቶ መስፍን በሕግና በታሪክ በመጀመርያ ዲግሪ እንዲሁም በሕዝብ አስተዳደር በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ አቶ መስፍን ስኳርና የደም ግፊት እንደነበረባቸው የተነገረ ሲሆን፣ ተንሸራተው ለመውደቅ በሽታቸው ያብቃቸው አያብቃቸው ግልጽ አልሆነም፡፡
የኢዴፓ መሥራች የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው አገሪቱ በአቶ መስፍን መሞት ትልቅ የፖለቲካ ሰው ማጣቷን ገልጸው፣ ‹‹እንደ አቶ መስፍን መንግሥቱ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በጥልቀት የተረዳ ሰው አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡
RIP!
ReplyDelete