Popular Posts

Wednesday, April 15, 2015

የአርባ ምንጭ ከተማ ህዝብ በመብራት መቆራረጥ የተነሳ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ እና ክርክር መከታተል አልቻለም ሲል ኢዜአ ዘገበ።

በተደጋጋሚ በተፈጠረ የመብራት መቆራረጥ ምክንያት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጉትን የፖሊስ ክርክር በሚዲያ መከታተል እንዳልቻሉ አንዳንድ የአርባምንጭና አከባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ። መብራት ኃይል በበኩሉ መብራት የተቋረጠው በቴክኒክና በነፋስ ምክንያት በተፈጠረ ችግር መሆኑን ገልጿል፡፡

   በአርባምንጭ ከተማ የሴቻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ መስፍን ካንኮ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ፓርቲዎች ባለፉት በሁለት መድረኮች በፖሊሲና ስትራተጂ ጉዳዮች ላይ ያደረጉትን ክርክር መብራት በመጥፋቱ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን መከታተል አልቻሉም። “የመድበለ ፓርቲ ስርዓት በኢትዮጵያ፤ “የፌዴራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የተደረገውን ክርክር መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ሙሉ ፕሮግራም መከታተል እንዳልቻሉ አቶ መስፍን ገልጸዋል። ፓርቲዎች ፊት ለፊት የሚያደርጉት ክርክር ከየትኛውም ዓይነት የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራሞች በተለየ ህብረተሰቡ የፓርቲዎችን የፖሊሲ አማራጮችን እንዲመዝን የሚያስችል መሆኑን ገልጸው “ካርድ በእጁ ይዞ ለምርጫ የሚዘጋጅ ህዝብ በጨለማ ውስጥ ሆኖ ይህን የመሰለ ፕሮግራም መከታተል አለመቻል ያሳዝናል” ብሏል።
  በሼቻ በቀለ ሞላ ሰፍር ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ዳልኬ በበኩላቸው በፓርቲዎቹ ክርክር የተደረጉ ሁለቱንም ፕሮግራሞች ለመከታተል ከፍተኛ ጉጉት እያላቸው በመብራት ችግር ምክንያት ሊከታተሉ እንዳልቻሉ ገልጸዋል። በአከባቢው ያለው ህብረተሰብ በአብዛኛው መረጃ የሚያገኘው በክልል ቴሌቪዥን፣ በኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎችና በኢትዮጵያ ብሮድካስትንግ ኮርፖሬሽን መሆኑን ገልጸው ይህ የፓርቲዎች ክርክር ከኢትዮጵያ ብሮድካስትንግ ኮርፖሬሽን ውጭ በሌሎች ኤፍ ኤምና በክልል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጭምር ሊተላለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል። አብዛኛዎችን አገራዊ ጉዳዮችን የሚከታተሉት በቴሌቪዥን መሆኑን የገለጹት ሌላኛዋ የከተማ ነዋሪ ወይዘሪት አበዛሽ ሰለሞን በበኩላቸው ፓርቲዎች በክርክር በሚያነሱዋቸው ጉዳዮች ላይ ህብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲያገኝ መደረግ አለበት ብለዋል። በምርጫው ለመሳተፍ ካርድ ይዘው ከፓርቲዎች አማራጭ በሚጠበቅበት በአሁኑ ጊዜ በሚዲያዎች በኩል የሚደርሱ ወሳኝ መረጃዎች በመብራት መጥፋት ምክንያት ሳያገኙ እንደቀሩ ገልፀዋል፡፡ ፓርቲዎች በፖሊሲና ፕሮግራሞች ላይ ያደረጉትን ክርክር በመብራቱ መቋረጥ ምክንያት መከታተል ባለመቻላቸው በሚዲያ ተቋማት በኩል ሁለቱም የክርክር መድረክ ፕሮግራሞችን እንደገና መከከታተል የሚችሉበት እድል እንዲመቻችላቸውም ጠይቀዋል።
   የኢትዮጵያ ኤሌክትርክ ኃይል ኮርፖሬሽን የአርባምንጭ ደንበኞች አገልግሎት ማዕከል ስራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ወንድምነህ በሰጡት ምላሽ መብራት የተቋረጠው በቴክኒክ ብልሽትና በነፋስ አማካኝነት የኤሌክትሪክ ተሸላሚ ምሰሶ በመውደቁ እንደሆነ ገልጸዋል። በነፋስ ምክንያት የተፈጠረው የመብራት መቆራረጥ ከአቅም በላይ በመሆኑ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ያልተቻለ ቢሆንም በትላንትናው ዕለት ለተፈጠረው ችግር አስቸኳይ መፍትሔ መስጠት ያልተቻለው ግን የወደቀውን የኤሌክትሪክ ተሸላሚ ምሰሶ ለማቆም በተሰማሩት ባለሙያዎች ላይ በአከባቢ የተወሰኑ ግለሰቦች በፈጸሙት ድብደባ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። በትላንትናው ዕለት በከተማው በተለምዶ ቴሌ ጀርባ በሚባል ሰፈር ከመብራት መቋረጥ ጋር በተያያዘ በነፋስ የወደቀውን የኤሌክትሪክ ተሸካሚ ምሰሶ ለማቆም በተሰማሩ ሦስት የመብራት ኃይል ባለሙያዎች ላይ ዛቻና የድብደባ ወንጄል መፈጸሙን ተናግረዋል። “እኛ ለዚሁ ፕሮግራም መስተጓጎል ሆን ብለን መብራት የሚናጠፋበት ምክንያት የለም” ያሉት ስራአስኪያጁ አጋጣሚ ሆኖ የፓርቲዎች ክርክር በሚካሄድበት ሰዓት ላይ መብራት በመጥፋቱ ከቸልተኝነት ጋር መያያዝ እንደሌለበት አስታውቀዋል።
 የአርባምንጨ ከተማ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ታደሰ በበኩላቸው ሁለቱም የፓርቲዎች ክርክር ሲካሄድ በከተማው መብራት በመቋረጡ ምክንያት ህብረተሰቡ ሚዲያ መከተተል ባለመቻሉ ያነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮግራሙም ሳይደገም በመቅረቱና በትላንትናው ዕለትም ተመሳሳይ ችግር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በጥቂት ግለሰቦች ቁጣን ያዘለ ድርጊት በመብራት ኃይል ባለሙያዎች ላይ መፈፀሙ አግባብ አለመሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ስሜት ውስጥ በመግባት በመብራት ኃይል ባለሙያዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ ጥቅት ግለሰቦች ጉዳይ እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment