Popular Posts

Friday, December 5, 2014

"አርባ ምንጭ የባከነ ጊዜዋን እያሰላች ለቀጣይ ስኬት መንደርደር ጀምራለች"

 



  "አርባ ምንጭ የባከነ ጊዜዋን እያሰላች ለቀጣይ ስኬት መንደርደር ጀምራለች"
 የከተማው መግቢያ በር አካባቢ አሁንም በግንባታ ማሽኖች ድምፅ እንደታጀበ ነው፡፡ ነዋሪውን ካማረሩ ጉዳዮች መካከል የዚህ መንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ አንዱ ነው፡፡ ከተጀመረ ሰባት ዓመት ያለፈው የሁምቦ አርባ ምንጭ መንገድ እስከ አሁን አለመጠናቀቁን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች ሳይቀሩ ይደነቁበታል፡፡ ወጣት በኃይሉ ከነዚህ የቀድሞ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአርክቴክት ሙያ የተመረቀው በኃይሉ የመንገዱን አለመጠናቀቅ ሲሰማ አሁንም ድረስ ይገርመዋል፡፡ ገና ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመድበው ሲሄዱ ጀምሮ እስከ ምርቃት ቀን ድረሰ የሁምቦ አርባ ምንጭ ጎዳና በከባድ አቧራ መታፈኑን በመሰልቸት ያስታውሳል፡፡ የወጣት አርክቴክት ሃሳብ ብዙዎች ይጋሩታል፡፡
መንገዱ አሁንም በብዙ ውጣ ውረዶች ታጅቦ፤ ሲጀመር ተይዞለት ከነበረው 340 ሚሊዮን ብር በጀት ወደ700 ሚሊዮን ብር በላይ ልቆ በቀጣዩ ዓመት መግቢያ ወራት ሊጠናቀቅ ተስፋ ተደርጎበታል፡፡ የጎልማሳነት ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው አርባ ምንጭ ከታደለችው የተፈጥሮ ሀብት ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ የመንገዱ አለመጠናቀቅ የኋሊት መጎተቱ እሙን ነው፡፡ በቅርቡ ሃምሳኛ ዓመት የምስረታ ሻማዋን ለመለኮስ የበቃችው ከተማ «ከዕድሜዋ ጋር የሚመጥን ደረጃ ላይ አትገኝም» ብሎ ለመደምደም ቢከብድም የሚገባት የዕድገት ደረጃ ላይ ላለመሆኗ ማሳያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ለምስረታዋ ሃምሳኛ ዓመት መከበር ምክንያት ከሆኑት መካከልም ባለፉት ዘመናት አንዴ ሞቅ ከዚያ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚለውን የለውጥ ሂደት ወጥ በሆነ መልኩ የዕድገት ሀዲድ እንድትጓዝ ነው፡፡
የበዓሉን መቃረብ አስመልክቶ በከተማዋ የነበረን ቅኝት በነዋሪው ምልከታ እና ትዝብት የታጀበ ነበር፡፡ ሁሉም ነዋሪ ከተማዋን በሚያይበት የራሱ መነፀር ባለፉት ዓመታት «ይሄ ለውጥ አለ» በቀጣይ ደግሞ «መለወጥ አለበት» ያሉትን አውግተውናል፡፡ ከከተማው አንደኛው ክፍል በተለምዶ ሴቻ ከሚባለው አካባቢ ያገኘነው ወጣት ዳንኤል ጎርፉ ከተማዋ ባለፉት ጊዜያት የሚጠበቅባትን ያህል በዕድገት መራመድ ባትችልም በተለይ ከሁለት ዓመታት ወዲህ መነቃቃት ታይቶባታል፡፡ የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መገንባት ለለውጡ አንድ ማሳያ አድርጎ ያነሳዋል፡፡ ነገር ግን ነዋሪው በከተማው ልማትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያሳየውን ቸልተኝነት መታዘቡን ይጠቅሳል፡፡
ልማቱ በህዘቡ ሙሉ ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት የሚያምነው ወጣት ዳንኤል «በልማት ዙሪያ ነዋሪው በጋራ መወያየት እና መስራትን ባህሉ ማደግ ይገባዋል» የሚል ሃሳብ ያንፀባርቃል፡፡ በተጨማሪም በከተማው በጥቃቅን እና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው በሚገኙ ወጣቶች ላይ የታዘበውን ጉዳይ ይናገራል፡፡ በርካታ ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ መኖራቸውን፤ ነገር ግን እነዚህ ወጣቶች ላይ ደካማ የቁጠባ ባህል ማስተዋሉን ያነሳል፡፡ ከወጣቶቹ በተጨማሪ ማህበራቱን በሚያደራጁት አካላት ላይ «የክትትል ማነስ ይታያል» ይላል፡፡ በቀጣይ ግን ራሱም የመደራጀት ፍላጎት እንዳለው በመጥቀስ አስተያየቱን ይቋጫል፡፡
በዚሁ አካባቢ ያነጋገርኳት ወጣት ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራች ናት፡፡ የቤተሰቧን ሆቴል በማስተዳደር ላይ የምትገኘው ወጣት ስሟን ከመግለፅ እንድቆጠብ ጠየቀችኝ፡፡ እንደ ፍላጎትሽ ይሁን ብዬ ወጋችንን ጀመርን፡፡ ወጣቷ በከተማው ውስጥ በርካታ ለውጦች ያስፈልጋሉ ትላለች፡፡ ለሃሳቧ መነሻ ያደረገችው ደግሞ ወደ ከተማዋ የሚያደርሰው መንገድ ለረጅም ጊዜ ተጓትቶ እስከ አሁን አለመጠናቀቁን ነው፡፡ በተጨማሪም በንግድ ቤቶች፣ በትራንስፖርት ዘርፍ ችግሮች መኖራቸውን ትናገራለች፡፡ በንግድ ቤት ላይ የሚቀመጠው ግምታዊ ግብር ለነጋዴው አለመመቸቱን ታስረዳለች፡፡ በዚህ ምክንያት ነጋዴው ዘርፍ በመቀየር ላይ መሆኑን ጠቁማለች፡፡
ወጣቷ በከተማው ባላት ቆይታ ካየቻቸው በጎ መሻሻሎች መካከል አርባ ምንጭን አቋርጦ የሚያልፈውን መንገድ ነው፡፡ እንዲሁም በአገሪቱ በተለይ በውሃ ዘርፍ ገናና የሆነው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መስፋፋት ታነሳላች፡፡ ይሄም በዘላቂነት ትኩረት ተሰጥቶት ሊቀጥል ይገባል ባይ ነች፡፡ በነጋዴው ላይ ከግብር ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመው ችግር መቀረፍ እንዳለበት ሃሳቧን ሰጥታለች፡፡ «በውሃ እና መብራት ላይ የሚታዩ መቆራረጦች ተደጋግመው ይታያሉ» የምትለው ወጣቷ፤ እንደሌሎቹ የከተማዋ ችግሮች ሁሉ በአገልግሎት አሰጣጥ በኩልም የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውን አስረድታለች፡፡ በተረፈ ግን የቱሪስት መዳረሻ የሆነችው ከተማ ከዘርፉ ይበልጥ እንድትጠቀም በፀጥታና ተያያዥ ችግሮች ላይ ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ ይገባል ትላለች፡፡
የዕድሜ ባለፀጋው አቶ ዋጌሾ ዋዛ የአርባ ምንጭ ከተማ አስራ አምስት ዓመት ታላቅ ናቸው፡፡ በዚህ ቆይታቸው ብዙ ነገር ታዝበዋል፡፡ ከተማዋ ጫካ ከነበረች ጊዜ አንስቶ በደንብ ያውቋታል፡፡ ታዲያ አሁን ያለው የከተማ ዕድገት፣ የመሰረተ ልማት መስፋፋት በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ከሌሎች መሰል ከተሞች ጋር ሲያወዳድሯት ለእርሳቸው አርባ ምንጭ አሁንም ብዙ ይቀራታል፡፡ «ድሮ እንድ እቃ አስር ብር ከገዛክ መርፌ ምርቃት ነበር፤ አሁን መርፌ በአቅሙ ተወዷል» የሚሉት አቶ ዋጌሾ፤ የኑሮ ውድነት የከተማው ነዋሪ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በቀጣይ የዚሁ ኑሮ ውድነት መረጋጋት ምኞታቸው ነው፡፡
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሽመልስ ታደሰ እንደሚሉት አርባ ምንጭ ዛሬ የደረሰችበት ደረጃ የአምሳ ዓመት ውጤት አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ «ከከተማዋ ምስረታ አንስቶ ባሉት ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ብዙ ለውጥ ሳታሳይ ቆይታለች» የሚሉት ከንቲባው፤ ዛሬ የሚታዩ የመሠረተ ልማትም ሆኑ ሌሎች ግንባታዎች የባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ጥረት ውጤቶች መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ በነዚህ ዓመታት ለውጦቿ በሌሎች ከተሞች እንደሚታየው ፈጣን መሆኑን ያነሳሉ፡፡ ከተማዋ ከተፈጥሮ መስህቦቿ ከምታገኘው የቱሪስት ገቢ በተጨማሪ በአትክልትና ፍራፍሬ አኮኖሚዋ ማገዝ ችላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይም የአባያ እና ጫሞ ሃይቅ ዋናው የቱሪስት መዳረሻ ያደርጓታል፡፡
እስከ አሁን አትክልትና ፍራፍሬ በቀጥታ ወደ ገበያ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን እሴት በመጨመር ወደ ገበያ ማቅረብ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ዕድሉ ክፍት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለይም ከንግዱ ማህበረሰብ የሚነሳው የግብር አሰባሰብ ሂደት ቅሬታ አስመልክቶ የግብር ግምት ትመናው ይበዛብናል የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ እንደሚነሳ አስታውሰው፤ በነጋዴው ዘንድ የተጨማሪ ዕሴት ታክስ ተመዝጋቢ ላለመሆን መፈለግ ስለሚስተዋል ይሄን ከማስተካከል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ «የግብር ተመን በዛብን» የሚሉት ግን በግብር ሕጉ መሰረት ይግባኝ ማለት እንደሚቻል አንስተዋል፡፡ የከተማዋን ከንቲባ በአባልነት የያዘ የነጋዴ ቅሬታ በአግባቡ የሚመለከት ኮሚቴም መቋቋሙንም አስረድተዋል፡፡
በከተማዋ ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት አስር ወራት ከ17 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን በማንሳት፡፡ በዚህም ከ114 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ዕድል የተመቻቸ ሲሆን ዘርፎቹም በማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ አገልግሎት እና ንግድ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በኮብልስቶን ንጣፍ በደቡብ ኦሞ ስኳር ልማት፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስፋፊያዎች ላይ የተሳተፉ አሉ፡፡ በቀጣይም ይሄ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በከተማዋ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም እና የኮንፍረንስ ማዕከል መሆኗን ይበልጥ ለማስተዋወቅ በቀጣይ ብዙ ይሰራል፡፡ ሃምሳኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት በዋናነት ለቀጣይ ስኬቶች መሰረት የሚጥሉ ተግባራት ይከናወንበታል፤ ከኢንቨስትመንቱ ባሻገር መልካም አስተዳደርን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ውይይቶች ይካሄዳሉ፡፡ በቱሪዝም፣ ግብርና እና ኢንዱስትሪ ላይ በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ጠቁመው፤ በኢንቨስትመንት በኩል እንደ ዞን በተለይም የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬዎች ላይ ዕሴት ጨምሮ ወደ ገበያ ማድረስ አሁንም ትኩረት ይፈልጋል፡፡
በከተማዋ ህዝብ ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጨምር የመንገድ ፍላጎት መኖሩን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ከመንገድ በተጨማሪ የውሃ እና የመብራት ፍላጎትም አድጓል፡፡ የነዋሪውን ፍላጎት ለሟሟላትም ከተማዋን አቋርጦ ከሚያልፈው ዋና መንገድ በተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ ግንባታዎች በመከናወን ላይ ቢገኙም፤ «ከከተማው አቀማመጥ ጋር ተያይዞ ግንባታዎቹ ፈታኝ ሆነው ቆይተዋል» ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሚያሰራው የሁምቦ አርባ ምንጭ መንገድ ግንባታ ከረጅም መጓተት በኋላ በተሰጠው ትኩረት በ2007 ዓ.ም መግቢያ ላይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ይበቃል፡፡
የከተማዋ ከፍተኛ ችግር ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነውን የድልድይ እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ ድልድዮች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ከተማዋ በበርካታ ሸለቆዎች ውስጥ እንደመገኘቷ እስካሁን ህዝብን ከህዝብ ለማገናኘት አስቸጋሪ የነበሩ አካባቢዎች በድልድይ እንዲገናኙ እየተደረገ ነው፡፡ ከፍሳሽ ማስወገድ ጋር በተያያዘ በከተማ ውስጥ 25 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ግንባታ ተከናውኗል፡፡ የንፁህ መጠጥ ውሃ በተመለከተ ለቀጣይ አርባ ዓመት ችግሩን ሊቀርፍ የሚችል ፕሮጀክት በበዓሉ ወቅት ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
አርባ ምንጭ ከተመሰረተች ሃምሳ ዓመት ቢሆናትም የከተማ መዋቅር የያዘችው በ1995 ዓ.ም የከተማ ልማት ፖሊሲ ሲተገበር ነው፡፡ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ታገሰ ጨፎ ባለፉት አስር ዓመታት በከተማዋ ዕድገት ላይ ረጅም ርቀት መሄድ ተችሏል ብለዋል፡፡ በመሰረተ ልማት እና በማህበራዊ አገልግሎት ተጨባጭ ለውጥ ታይቷል፡፡ ከተማዋ ለባለሀብቱ ምቹ መሆኗን አስመልክቶ «በትንሽ ጥረት ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚቻልባት» ሲሉ ይገልጿታል፡፡ እንደርሳቸው አሁን ያለው ፈጣን ዕድገት ይዞ መጓዝ ከተቻለ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የተመዘገበውን ልማት በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ለማምጣት የሚያስችል መሰረት መጣሉን ነው፡፡
የሆነው ሆኖ አርባ ምንጭ ያለፉ ዘመኖቿን በቁጭት እያሰበች ለወደፊት ስኬት ሞራል ሰንቃለች፡፡ ከተማዋን ከሁለት የባህር ማዶ ከተሞች ጋር በእህትማማች ከተማ የማስተሳሰር ስራ መጀመሩን የከተማዋ ከንቲባ ገልጸዋል፡፡ ከአምሳ ዓመት በፊት በወቅቱ አካባቢውን ያስተዳድሩ የነበሩ አዕምሮ ሥላሴ የተባሉ ሰው ከጨንቻ ወደ ጊዶሌ ሲሄዱ በማየታቸው አካባቢው የጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ እንድትሆን መምረጣቸውን ከንቲባው ነግረውናል፡፡ ከተማዋ በተፈጥሮ ሀብቶቿ በተለይም በአባያ እና ጫሞ ሃይቆች የምትታወቅ ሲሆን ነዋሪዎቿም አስክ 103 ሺ ይገመታል፡፡
Details
Published Date
Written by ብሩክ በርሄ
Category: ፖለቲካ
Add comment

No comments:

Post a Comment