Popular Posts

Wednesday, December 3, 2014

በአርባ ምንጭ ከተማ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የገበያ ማእከል ተገነባ
 አርባምንጭ ህዳር 21/2007 በአርባምንጭ ከተማ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ለአገልግሎት መዘጋጀቱን የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታውቋል።
 የገበያ ማእከሉ በአርባምንጭ ከተማ በተበታተነ መንገድ ሲካሄድ የቆየውን የግብይት ስርዓት ወደ ዘመናዊ አሰራር ይቀይራል ተብሏል፡፡
 በአርባምንጭ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ታምሩ ታደሰ ትላንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የገበያ ማዕከሉ የተገነባው የከተማው መሪ ፕላን በሚፈቅደው መሰረት ለንግድ ማስፋፊያ በተለዩ ሁለት አከባቢዎች ነው።
 በከተማው አሁን በስራ ላይ ያሉት የገበያ ቦታዎች የተበታተኑና ለዘመናዊ ንግድ ስራ የማይመቹ ከመሆናቸውም በላይ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችና ሌሎች ሸቀጦች ተቀላቅሎ የሚገበይበት ነው፡፡
 ይህንን ስርዓት በአዲስ መልክ ለመቀየር ከተማ አስተዳደሩ 344 ሱቆችና 33 ሸዶች ያሉባቸው ሁለት ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ገንብቶ ለአገልግሎት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
 ገበያ ማዕከሉ በዋናነት የኢንዱስትርና የጨርቃጨርቅ ምርቶችና ሌሎች ሸቀጦች የሚገበያዩበት ነው፡፡
 ከግብይት ሱቆቹ መካከል 144 የሚሆኑት በህጋዊ ጨረታ ለንግዱ ማህበረሰብ እንደሚተላለፉና 200 በላይ ሱቆች በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዝ ለተደራጁ ማህበራት በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚቀርብላቸውም ገልጸዋል።
 በነባሩ ሼቻና ስቀላ ገበያ ማዕከል የንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ ነጋዴዎች መካከል አንዳንዶቹ የገበያ ማዕከሉ አሁን በከተማው ውስጥ የሚታየውን የተበታተነውን የንግድ ስርዓት ዘመናዊ ከማድረግ አንጻር የተሻለ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
 ከነጋዴዎቹ መካከል አቶ የሱፍ አብዱልአዚዝና ወጣት ማሙዬ ሰይፉ እንደተናገሩት ዘመናዊ የገበያ ማዕከሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የብዙ ነጋዴዎችን የንግድ ቦታና የቤት መጣበብ ችግር ይፈታል።
 ገበያ ማዕከሉ የተሟላ መሰረተ ልማት ያለው መሆን እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀው የገበያ ማዕከሉ የተገነባበት ቦታ ከተለመደው የግብይት ማዕከል ወጣ ያለ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ የመንገድ፣ መብራት፣ ትራንስፖርትና ውሃ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን አስቀድሞ ማመቻቸት እንዳለበት ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment